- እስራኤላውያን እግዚአብሄርን ቢበድሉም እንኳን ለቃልኪዳን ልጆቹ አዘነላቸው፣ ራራላቸው። እውነተኛ ንስሀ ሁልጊዜ የእግዚያብሄርን ቁጣ ያበርዳል/ይከለክላል (መሳ 10:16)።
- የእግዚአብሔር ምህረት ወይም የማዳን ፀጋው ከቁጣው ትበልጣለች (ሰቆ 3:22፣ ሮሜ 5:20-21)።
- እግዚአብሔር ሁልጊዜ ለህዝቡ ታዳጊ፣ ጠባቂ መስፈን ያስነሳል (ሐዋ 4:11-12፣ ማቴዎስ 2:5-6)።
- እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከጉስቁልናቸው ለመታደግ አንድ አዳኝ (መስፍን) ሊያስነሣ በወደደ ጊዜ ምርጫው ዮፍታሄ ነበረ። ዮፍታሄም በወንድሞቹ ከአባቱ ቤት የተገፋ ነበረ (መሳ 11: 3)። በፊቱ የታመነለትና ሁኔታውን የተመለከተ እግዚአብሔር ግን በጠሉት ፊት በራሱ ጊዜ አለቃ/ ራስ አድርጎ ሾመው (መሳ 11: 7-8፣ 11)።
- ዮፍታሄ ጽኑ አና ሀያል ሰው ቢሆንም እንኳ በራሱ አቅም እስራኤልን አልታደገም። ዮፍታሄ የተሰጠውን ተልዕኮ በእግዚአብሔር መንፈስ ተወጣ (መሳ 11:29)። ያለ መንፈስ ቅዱስ ምንም አይነት የእግዚአብሔርን ስራ መስራት አይቻልም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን አገልግሎቱን የጀመረውና የጨረሰው በእግዚአብሔር መንፈስ ነው (ኢሳ 61:1)።
- ዮፍታሄ የአሞናውያን ንጉስ ያላግባብ በተቃወመው ጊዜ በመካከላቸው እንዲፈርድ ጉዳዩን ለእግዚአብሔር ሰጠው። እኛም የሚጋፉን ሰዎች ለእግዚአብሔር መተው ያስፈልገናል (መሳ 11:27)።
- ዮፍታሄ ለእግዚአብሔር ታማኝና ታዛዥ ነበረ (መሳ 11:30-31፣39)።
- ለእግዚአብሔር ወይም ለሰዎች ቃል ከመግባታችን በፊት የምንናገረውን በጥንቃቄ መምረጥ አለብን (መሳ 11:34-36)። አንዴ ከአፋችን የወጣ ቃል ባለዕዳ ያደርገናልና።