መልካም  ፍሬዎች 

መልካም  ፍሬዎች 

በፓስተር መስፍን ጥላዬ , Sep 8, 2024

  • እግዚአብሄር አብ እኛ ብዙ ፍሬ ስናፈራ እና የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ስንሆን ይከበራል (ዮሐ 15:8)።
  • የአንድ ክርስቲያን ዋናው የህይወት ግብ  እግዚአብሔርን ማክበር ሲሆን (1 ቆሮ 10:31) ኢየሱስ ራሱ  የአገልግሎቱ መደምደሚያ አድርጎታል (ዮሐ 17:4)።
  • ብዙ ፍሬ ማፍራት የጥረት ውጤት ሳይሆን ከኢየሱስ  ተጣብቆ የመኖር ትርፍ ነው (ዮሐ 17:4-5)።
  • እግዚአብሔር አብ በእኛ ህይወት ያለመታከት ቀን እና ማታ በሚሰራ ገበሬ ይመሰላል (ዮሐ 15:1)።
  • አብ ከህይወታችን ፍሬ የሚጠብቀው የሚያስፈልገንን መነሻ ግብዓቶች ሁሉ አስቀድሞ ሰጥቶን ነው (ኢሳ 5:1-6፣  1 ጴጥ 1:3)።
  • እግዚአብሔር በህይወታችን እንድናድግና እንድናፈራ የሚሰጠን ዘር ቃሉን ነው (ሉቃ 8:11)።
  • የእኛም ልብ አራት ልዩ ልዩ መሬቶችን ሊመስል ይችላል። እነዚህም:-

ሀ) በመንገድ ዳር ያለ መሬት (ሉቃ 8:12)- ይህ ያልተከለለ፣ ጥበቃ የሌለው፣ ሁሉም ነገር ሳይመረጥ የሚገባበት ልብ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ቢሰማም ዲያቢሎስ ቃሉን ከዚህ አይነት ልብ ይወስደዋል።  ፍሬያማነት እግዚአብሔር በቀጠረልን ስፍራ መገኘትን ይጠይቃልና።

ለ) በዓለት ላይ ያለ መሬት (ሉቃ 8:13)- ይህ ጠንካራ ልብ ሲሆን የሚሰማውን የእግዚአብሔር ቃል ለጊዜው ብቻ  በደስታ ይቀበላል።  ለእግዚአብሔር ቃል የማይሰበር ድንጋይ ልብ ስለሆነ (ኢሳ 66:2) ፈተና ሲመጣ በርትቶ መቆም የሚችልበት ስር የለውም።

ሐ) እሾሃማ መሬት (ሉቃ 8:14)- ይህ ሁሉንም ፈላጊ ልብ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ቢቀበልም ከስጋ ፈቃድና እግዚአብሔርን ከሚያሳዝን ኃጢአት ጨክኖ  መለየት አይችልም።  ስለዚህም ክፉ ዘር አድጎ መልካሙን ያንቀዋል። 

መ) መልካሙ መሬት  (ሉቃ 8:15)- እነኚህ  የእግዚአብሔር ቃል በበጎ ልብ፣ በትህትና የሚቀበሉ፣ ሰምተውም የሚጠብቁ፣ በመከራም መሃል የሚጸኑ ናቸው።

እግዚአብሔር  በህይወታችን እንዲከበር  በእኛ ውስጥ የሚጠብቃቸው  አራት ፍሬዎች:

  • የጽድቅ ፍሬ (ፊሊ 1:9)- እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ከኩነኔ የፀዳ ህይወት ስለ ሰጠን የምንኖረው ህይወት የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያሳይ፣  ያለነውር የሆነ፣ በሰዎች ዘንድ በመልካም ምስክርነት የተሞላ መሆን አለበት።
  • የብርሃኑ ፍሬ (ኤፌ 5:8-11)- ማንነታችን ብርሃን ስለሆነ ከአለም ጨለማ ተለይተን በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ልንራመድ ይገባል።
  • የበጎ ስራ ፍሬ (ቆላ 1:9-12፣ ማቴ 5:16)-   በኢየሱስ የመስቀል ስራ የተወለደውን አዲሱን ማንነታችንን በበጎ ስራ ሁሉ  እንድናጎለብተው ይጠበቅብናል።
  • የመንፈስ ፍሬ ( ገላ 5:22)- መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን የክርስቶስን ባህሪያት ዕለት ዕለት እየገለጠ አብን የሚያከብርበት መንገድ ነው።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *