By Pastor Mesfin Tilaye, August 4, 2024
- ኢየሱስ በሰማርያ በቀትር ጠራራ ፀሐይ እንዲያልፍ ያደረገው ዓላማ እና ፍቅር ነው (ዮሐ 4:1-10)።
- የህይወት እንጀራ የሆነው የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልቀጠረችውን አንዲት ሴት ይጠብቅ ዘንድ እርሱ ሰው ሆኖ መድከምን፣መጠማትን፣መራብን ተቀበለ (ዮሐ 4:6፣7፣8)።
- ኢየሱስ ሳምራዊቷ ሴት ወንጌልን እንድታገኝ እንቅፋት የሆኑባትን አራት ግርግዳዎች አፈራርሷል።እነዚህም-
ሀ) የጥል ግርግዳ (ዮሐ 4:9)- አይሁዶች ሰማርያውያንን የመናፍቃን ትምህርትን ያስተምራሉ፣ ደግሞም በዘራቸው ከአህዛብ ጋር ተደባልቀዋል ብለው እንደ እርኩስ ህዝቦች ይቆጥሯቸው ነበር (1 ነገ 17)።
- ገና ተስፋ ያጣን በነበርን ጊዜ ኢየሱስ በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የጥል ግርግዳ በሰውነቱ አፍርሶ በመስቀሉ ገድሎ አስታረቀኝ (ኤፌ 2:11-19)።
ለ) የፆታ ግርግዳ (ዮሐ 4:9)- በአይሁድ ባህል ለሴቶች የሚሰጠው ማህበራዊ ዋጋ ዝቅተኛ ስለነበረ ወንዶች ሴት ሆነው ባለመፈጠራቸው እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበረ። ከዚህም የተነሳ አንድ አይሁዳዊ ወንድ በአደባባይ ከሴቶች ጋር ሲነጋገር መታየት አይፈልግም ነበር።
- ሴቶች (አህዛብ ሴቶችን ጨምሮ) የኢየሱስ የዘር ሐረግ (ለምሳሌ ትእማርና ሩት) እና የአገልግሎቱ ደጋፊዎች (ለምሳሌ መቅደላዊት ማርያምና ማርታ) ነበሩ።
ሐ) የሞራል ግርግዳ (ዮሐ 4:9-19)- ሴቲቱ በሰው ፊት የተገለጠ የሞራል ችግር ስላለባት ሌሎች ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የማይመጡበትን የቀትር ሰዓት ጠብቃ ወደ ውሃ ጉድጓድ ትመጣ ነበር።
- ኢየሱስ በሰዎች ውስጥ ያለውን የኃጢአት ምንጭ ሳይነካ ወደ ራሱ አምጥቶ አያስቀረም።
- ሰው የማይነካው የሞራል ውድቀት በኢየሱስ ሲነካ ሰዎች ኢየሱስን እንደ አንድ ታላቅ ሰው ወይም ነቢይ ብቻ አርጎ ማየት አቁመው ጌትነቱን ይቀበላሉ።
መ) የሐይማኖት ግርግዳ (ዮሐ 4:20-24)- በአይሁዶች እና በሰማርያውያን መካከል እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ወይስ በገሪዛን ይመለካል የሚል ጽንፈኝነትን የተሞላ የእምነት ልዩነት ነበረ።
- ኢየሱስ እግዚአብሔር አብ የሚመለከው በመንፈስና በእውነት ብቻ እንደሆነ ገለጠ።
- ሴቲቱ የኢየሱስን ማንነት ተረድታ የህይወት ምንጭ ውሃ ከውስጧ በፈለቀ ጊዜ መጀመሪያ የመጣችበትን አጀንዳ (የድሮ ታሪኳን እና ቀዳሚ ጉዳዮችዋን) ትታ ስለእርሱ ልትናገር ሄደች (ዮሐ 4:27)።
- ለሳምራዊቷ ሴት የምታፍርበት ነገር የምትናገርበት የምስክርነት ምንጭ ሆነላት። ከሆዷ የሚወጣው የህይወት ምንጭ ውኃ ለእርስዋ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎችም የሚተርፍ ሆነ። ይንቋት የነበሩት ሰዎች እርሷን ሰምተው ወደ ኢየሱስ መጡ፣ በእርሱም አመኑ (ዮሐ 4:30፣39-40)።
- እኛስ ዛሬ ረሀባችን፣ የነገራችን ምንጭ፣ እርካታችን የሆነው ኢየሱስ ወይስ በእጃችን የያዝናቸው ነገሮች ናቸው? (ኤር 2:13)