በወንድም ቢንያም እውነቱ , August 18,2024
የዚህ ሳምንት መልዕክት (1ኛ ተሰ 5:19) በተሰጠው ትእዛዝ ላይ የሚያጠነጥን ነው።ይህ ትእዛዝ የተሰጠው በእምነታቸው ጽናት፣ በስራቸው፣ እንዲሁም ጌታን በመምሰላቸው ለሌሎች ምእመናን መልካም ምሳሌ ተደርገው ለተጠቀሱ በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ለተሞሉ የተሰሎንቄ አማኞች ነው (1ኛ ተሰ 1:2-10)። ይህ የሚያመላክተው የትኛውም አማኝ የመንፈስ ቅዱስን እሳት የማቀጣጠል ወይም የማዳፈን አቅም እንዳለው ነው።የመንፈስ መቀጣጠል ከጥንት የነበረ የእግዚአብሔር ሀሳብ ነው (ዘሌ 6:10-13)።
በአርቲፊሻል መንገድ የመንፈስን እሳት ማቀጣጠል አይቻልም። በዚህ መንገድ የሚጀምር እሳት ብልጭ ብሎ ወዲያው ድርግም ይላል።
ታድያ መንፈስ እንዴት ይዳፈናል?
ሀ) መዋቅራዊ ችግር: መንፈስ ቅዱስ በአሁኑ ዘመን እንደቀድሞ የጸጋ ስጦታዎችን ለቤተ ክርስቲያን በማደል አይሰራም የሚል ስነ-መለኮታዊ እይታ። ይህንን ሃሳብ ለመደገፍ 1 ቆሮ 13:8-10 በተሳሳተ መንገድ ይጠቀሳል።
ለ) ንቀት: የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሰዎች ላይ ሲገለጥ የተነካው ሰው ሊኖረው የሚችለውን ምላሽ ተመልክቶ የእግዚአብሔርን ስራ ለራስ እንደማይመጥን ነገር መቁጠር(ሐዋ 2:13)
ሐ) በአመክንዮ አስተስሰብ መያዝ:- የመንፈስን ስራ መለኮታዊ በሆነ መንገድ ከመረዳት ይልቅ አማራጭ ማብራሪያ ወይንም አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ለመጠቀም መሞከር (ሐዋ 2:7-8)
መ) መታከት: የማያቋርጥ መንፈስ ቅዱስን ፍለጋ ማጣት
ሠ) ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት ያለመሆን መንፈስ ቅዱስ በእኛ ቀጠሮ አይሰራም። እርሱ ወዶ በህልውናው ሙላት በመካከላችን በተገለጠ ጊዜ እንደሚገባ፣ ከአቀድነው ፕሮግራም ውጪ እሱን ለማስተናገድ ፈቃደኝነት ማጣት
እነዚህን ተግዳሮቶች ከማሸነፍ ውጪ በጉባዔ መካከል ከልብ የሆነ መቀባበል የመንፈስ ቅዱስን እሳት ያቀጣጥላል። ይህም ማለት በተናጋሪው እና በሰሚው፣ በመሪውና በተማሪው መሃል መንፈስ ቅዱስን የመራብ አንድነት ሲፈጠር እግዚአብሔር አቅራቦትና ፍላጎትን አገጣጥሞ የመንፈስ ቅዱስን እሳት በኃይል እንዲነድ ያደርጋል።