አንዳንድ ጊዜ በእራሳችን ስራ ወይም አቅም ለመታመን እንፈተናለን። ጴጥሮስ ሌሎች ኢየሱስን ጥለዉ ቢሄዱ እንኳን እርሱ ከቶ እንደማይሰናከል እርግጠኛ ነበረ (ማቴ 26:33)። ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ እንደእርሱ እርግጠኛ ነበሩ(ማቴ 26:35)። ነገር ግን የፈተና ቀን በመጣ ጊዜ ልክ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረዉ (ማቴ 26:31) ሁሉም ጌታን ጥለዉ ሸሹ (ማቴ 26:56)።
- ማናችንም ነገ በእግዚአብሔር ፊት ስለሚኖረን አቋም በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። በእግዚአብሔር ቤት የምንዘልቀዉ በእርሱ ፀጋ እና ምህረት ብቻ ነዉ (ኢሳ 42: 3)።
- ኢየሱስ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ፈርተዉ፣ በክህደታቸዉ ተሸማቀዉ፣ ተረብሸዉ፣ በራቸዉን ዘግተዉ በተቀመጡበት ኢየሱስ መጣ (ዮሐ 20:19)።
- የኢየሱስ መምጣት ሰላምን (ይቅርታን እና ቅቡልነትን) ሰጣቸዉ (ዮሐ 20:19)። መለኮታዊ ደስታን እና ተልእኮን የሚያድስ ሰላምንም ጨመረላቸዉ (ዮሐ 20:20-21)። ለነዚህ ደካማ ሰዎች ተስፋ ቀጠለላቸዉ።
- ኢየሱስ ዳግመኛ መጣ። ኢየሱስ ጠያቂዉን ቶማስ (ዮሐ 20:26) እና በአደባባይ የካደዉን ጴጥሮስን (ዮሐ 21:4) ፍለጋ ደግሞ መጣ።
- ተልዕኮዋቸዉን ጥለዉ እንደገና ወደ ድሮ ስራቸዉ ተሰማርተዉ በከንቱ በደከሙ ጊዜ ኢየሱስ በአባትነት መንፈስ ቀረባቸዉ (ዮሐ 21:5)። የእግዚአብሔር ፍቅር፣ ያገኘነዉ የልጅነት ማዕረግ በድካማችን አይለወጥም።
- ጌታ አሁንም እንደበፊቱ ተዐምርን እንደሚሰራ ለደቀ መዛሙርቱ ባሳያቸዉ ጊዜ እንደቀድሞዉ ከእርሱ ለመለየት ከመሞከር ይልቅ ( ሉቃ 5:8)፣ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ፈጠነ (ዮሐ 21:7)።
- ኢየሱስ ለጴጥሮስ አቅሙ እስከየት ድረስ እንደሆነ ካሳየዉ በኋላ የአገልግሎት አደራ ሰጠዉ (ዮሐ 21:15-17)። እግዚአብሔር ጥሪን የሚያድስ፣ የፍቅርንም አገልግሎት የሚቀበል አምላክ ነዉ።
- እግዚአብሔር አደራን መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ መጨረሻችንን ያዉቃል፤ ደግሞም ያሳምረዋል (ዮሐ 21:18)።
- ጥሪያችን አንድ ነዉ። እርሱም ጌታችንን ኢየሱስን መከተል ነዉ።