ሐና እና  እናትነት- By Pastor Mesfin Tilaye, May 12, 2024

ሐና እና  እናትነት- By Pastor Mesfin Tilaye, May 12, 2024

  • ሐና የፀሎት ሴት ነበረች (1 ሳሙ 1:9-16)። የእርስዋ መፍትሄ በባሏ እጅ ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ታዉቅ ስለነበረ 

(ሀ) ኀዘንዋን፣ ጭንቀትዋን፣ ምሬቷንና ሸክሟን በእግዚአብሔር ፊት ጣለች (1 ሳሙ 1:10)። 

(ለ) እራስዋን አዋርዳ በትህትና ትፀልይ ነበረ (1 ሳሙ 1:11)። 

(ሐ) እግዚአብሔር የጠየቀችዉን እስኪመልስላት ድረስ ሳታቋርጥ ትፀልይ ነበረ (1 ሳሙ 1:12)።

(መ) በልቧ ትፀልይ ነበረ (1 ሳሙ 1:13)። በዉሰጥዋ ያለዉ እዉነታ በእግዚአብሔር ዘንድ ይሰማ ነበር። 

(ሠ) በቃልኪዳን የምትፀልይ ሴት ነበረች (1 ሳሙ 1:11)። 

  • ሐና ከፀለየች በኋላ በእግዚአብሔር ልብዋን አሳረፈች (1 ሳሙ 1:17-20)። የፀሎትዋን መልስ ሳትቀበል በፊት እግዚአብሔር እንደሰማት አምናለች። እኛም የሐናን ፈለግ ተከትለን በእግዚአብሔር ማረፍ ካልቻልን፣ መጨነቃችን ጉዳዩን በእርሱ ፊት እንዳልጣልነዉ ምልክት ነዉ።
  • ሐና ልጅዋን ኮትኩታ አሳድጋ ለአገልግሎት የምታበቃ እናት ናት (1 ሳሙ 1:21-24)። ሳሙኤልን ጡት አስክታስጥለዉ ድረስ (ገና ለጋ እድሜ ላይ ሳለ) ተንከባክባ አሳድጋ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት አብቅታዋለች። 
  • ሐና በየዓመቱ የልጅዋን እድገት ሳትታክት ትከታተል ነበረ  (1 ሳሙ 1:18-19)። ሌላ አምስት ልጆች ብትወልድም እንኳ ሳሙኤልን ከመከታተል ወደኋላ አላለችም። 

 በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን እንዴት እንፍታ?    በወንድም ቢንያም እውነቱ  May 19, 2024

  • ሉቃስ በሐዋርያት 6:1-6 በኢየሩሳሌም ያለችዉ ቤተክርስታይን ለናሙና አቅርቦ በዉስጥዋ ያቀፈቻቸዉ አማኞች ይዘዉት የመጡትን አርቲፊሻል ግርግዳ እንዴት በወንጌል ተሰብሮ ሁሉንም መሰብሰብ እንደተቻለ ያሳየናል። 
  • በዚህች ቤተክርስታይን ዉስጥ ዕብራዊያን አይሁዶች እና ግሪካዊ አይሁዶች አብረዉ ጌታን ያመልኩ ነበረ። ነገር ግን የቋንቋ፣ የዜግነት፣ የባህል እና የእሴት ልዩነቶች አብረዉ ዘልቀዉ ገብተዋል። ግሪካዊ አይሁዶች በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማደል አሠራር ላይ ከእነርሱ ወገን የሆኑት መበለቶች ችላ በመባላቸዉ በዕብራዊያን አይሁዶች ላይ አጉረመረሙ (ሐዋ 6:1)። 

ሀዋርያቱ ለቀረበዉ ፅኑ ቅሬታ ከሰጡት መልስ እኛም በቤተሰብ አልፎም በቤተክርስታይን ከልዩነት ለሚመነጩ ጥያቄዎች ምን አይነት ምላሽ መስጠት እንዳለብን እንማራለን። ይኸዉም- 

  1. የእግዚአብሔርን ቃል ጥናትና ፀሎት ችግሩን ለመፍታት ተብሎ መቆም የለበትም (ሐዋ 6:2፣4)።
  2. ለችግሩ ተመጣጣኝ መልስ መስጠት ያስፈልጋል (ሐዋ 6:3)። ሀዋርያቱ ዕብራዊያን አይሁዶች ቢሆኑም እንኳ ወገንተኝነት ሳይዛቸዉ፤ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰዎች እንዲመረጡ ትዕዛዝ ሰጡ። በመሆኑም ሰባቱም የተመረጡት ሰዎች ግሪካዊ አይሁዶች ነበሩ። 
  3. ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚመነጭ መልስ ልብን ያሳርፋል (ሐዋ 6:5)። ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ ጥበብ መሪዎች መፍትሄ እንዲሰጡ፣ ህዝቡ እንዲቀበልና መሪዎች ዉሳኔዉን እንዲያፀኑ መቀባበልን ያስችላል። የዉሳኔዉ ትክክለኛነት በፍሬዉ ይታወቃል (ሐዋ 6:7-8)።
  • የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን በአገልጋይ ዪናታን ሰለሞን June 2, 2023

በዚህ ሳምንት ጳዉሎስ በቆሮንቶስ ላለችዉ ቤተክርስቲያን የፃፈዉን የመጀመሪያ መልዕክት ጠቅለል አድርገን በመመልከት እኛም ያለንን  አቋም እንፈትሻለን። 

  1. የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ማናት? 

ሀ) ከቆሮንቶስ ከተማ አንፃር ስንመለከት: አካያ በሚባል አዉራጃ አቴንስን ከመሰሉ ዋና ከተሞች ጋር የምትመደብ፣ ትልቅ የህዝብ ቁጥር ያላት ቦታ ነበረች። የፖለቲካ አስተዳደር መቀመጫ እና በመልክአዊ ምድራዊ አቀማመጥ በብዙ ከተሞች የተዋሰነች ማዕከላዊ ስፍራ ናት። ከተማይቱ በቤተ ጣዖቶቿ ብዛትና በስካርም ትታወቃለች። 

ለ)  በክርስቶስ አካል ካላት ቦታ አንፃር: ባለቤትነቱ  የእግዚአብሔር የሆነች፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የተቀደሰች፣ በንግግር ሁሉ፣ በዕውቀትም ሁሉ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ስጦታ በክርስቶስ የበለፀገች ቤተክርስቲያን ናት (1 ቆሮንቶስ‬ ‭1‬:‭2‬ ፣ 4-7‬)። የነበሩባት ችግሮች ማንነቷን አልቀየሩም።

  1. በቤተክርስቲያኒቷ የነበሩት ዋና ዋና ችግሮች ምንድናቸዉ? 

ሀ) የመጡበትን ባህል፣ ዘር ወይም የመሪዎችን እና የጌታን ስም ተመርኩዘዉ መከፋፈል (1 ቆሮንቶስ‬ ‭1‬:‭2‬4፣ 1:11፣ 9:20፣ 10:32፣ 12:15-17፣ 21)። 

ለ) የስነምግባር ብልሹነት- የከተማዉ ክፋ ተፅዕኖ (ዝሙት፣ እርስ በእርሰ መካሰስ) በቤተክርስቲያኒቷ ዉስጥ ተንሰራፍቷል (1 ቆሮንቶስ‬ ‭5፣ 6) 

ሐ) አምልኮተ ስነስርዓቱ መንገድ ስቷል- የፀጋ ስጦታ አስተዳደር እና የጌታ እራት ስርአት ላይ ችግር ይታያል  (1 ቆሮንቶስ‬ ‭11: 20-22) 

መ) የአስተምህሮት ችግር (1 ቆሮንቶስ‬ ‭15)

  1. ሐዋርያዉ ጳዉሎስ ለእነዚህ ችግሮች ምን አይነት ምላሽ ሰጠ?

ሀ) የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ (1 ቆሮንቶስ‬ ‭1:26፣ 4:1፣ 9:24) 

ለ) ሁሉ ነገር (አምልኮተ ስነስርዓቱን ጨምሮ) በአግባብና በፍቅር ይሁን (1 ቆሮንቶስ‬ 14:37-40) 

ሐ) የምታደርጉት ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን። ይኸዉም ለሰዎች ማሰናከያ ከመሆን ተጠበቁ  (1 ቆሮንቶስ‬ 10:31፣ 33) 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *